መግፋት
መግፋት “rejection” ማለት አንድን ሰው ወይም ሌላን ነገር የእኛ አካል ወይም አባል እንዳይሆን ማድረግ ነው፡፡ የሰው ልጅ በተለያዬ ጊዜ በተለያዬ ሀገር በተለያዬ ምክንያት ሲገፋ የኖረ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ የተለያዬ አመለካከትና ባህሪ እንዲኖረው አድርጎራል፡፡ ይህ መገፋት ይዘቱና ጉዳቱ የተለያዬ ቢሆንም አሁንም ድረስ በሁላችንም ላይ እየደረሰ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በወላጅ እናትና አባታቸው፣ በወንድም እህታቸው፣ በፍቅር አጋራቸው፣ በልጆቻቸው፣ በጎረቤት ሰዎች፣ በጓደኖቻቸው የመገፋት ህመም ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡ ይህ መገፋት በሰው ላይ ሲደርስ አዕምሮን አዛብቶ አመለካከትን ቀይሮ ነው የሚሄደው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ሁሉም ሰው እያቀረበውና እያቀፈው የሚፈልገውንም እያሟሉለት ያደገን ልጅና በተቃራኒው ደግሞ በሁሉም ነገር እየተገፋ ያደገን ልጅ የሚኖራቸውን ሁሉን አቀፍ ልዩነት መመልከት ይቻላል፡፡
መገፋት ለአዕምሮ ቁስል የሚዳርግ አደገኛ ነገር ነው፡፡ አንድን ሰው እጁን በብረት መትተህ ልትሰብርበት ትችላለህ፡፡ እግሩንም እንዲሁ፡፡ እንዲገፋና እንዲጠላ አድርገህ አዕምሮውን ልትበርዝበትም ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ይህንን ሰው ለጉዳት የሚዳርገው ቃል ከአፍህ ሳይወጣ በመግፋት ብቻ ያሳየኸው የአዕምሮው ጉዳት ነው፡፡ ይህንን መገንዘብ ባለመቻላችን ለአዕምሮ ጉዳት ብዙ ትኩረት አንሰጠውም፡፡ ለእጁ ስብራት ግን ካሳ ልንሰጠው እንችላለን፡፡
ሰዎች እንዲፈሩ፣ በስራቸው እንዳይተማመኑ፣ ንግግራቸው ውበት እንዳይኖረው፣ ለነገር ለጥላቻ ቅርብ የሚሆኑት፣ ተንኮልና ምቀኝነት የሚሰሩት ስለተገፉ ነው፡፡ ትዳራቸውን ጠበቅ ማድረግ የተሳናቸው፣ በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ መሳተፍ የማይወዱት፣ በስራ ገበታቸው ላይ በሰዓት ገብተው በሰዓት የማይወጡት በአንድም በሌላም ምክንያት የመገፋት በደል ስለደረሰባቸው ነው፡፡ መገፋት አንድ ጊዜ ተከስቶ ከጊዜ በኋላ ልክ እንደ ሌላ ህመም የሚጠፋ አይደለም፡፡ ጦሱ እረጅም ጊዜ ሄዶ ለልጅም መድረስ የሚችል በመሆኑ ከአሁኑ ሰዓት ጀምረን መገፋት በማንም ዘንድ እንዳይኖር መታገል አለብን፡፡
እረኛዬ ተከታታይ ድራማ ሊነግረን ካሰበው ብዙ ቁምነገር መካከል አንዱ መገፋትና መግፋት የሚያመጣውን ችግር ነው፡፡ አስተውለን ከሆነ አህታችን ወጋየው እዚህ ሁሉ ጣጣ የገባችው የሚገፋት በመኖሩ ነው፡፡ ለትምህርት ብላ ወጥታ ፀንሳ ስትመለስ የሆነችውን ሁሉ መናገር ያልደፈረችው ከሚረዳት ይልቅ የሚገፋት በመኖሩ ነበር፡፡ እርግዝናዋ እንኳን ከፍ እያለ ሲመጣ በልብስ መሸፈን ነበር ተሸሎ የታያት አማራጭ፡፡ ወልዳ እንኳን ገና የሚፈሳት ደም ሳይደርቅ ከቤት እንድትወጣ ሆነ፡፡
ከዚያም ህይወቷ በሰቀቀን በፍርሃትና በስቃይ የተሞላ ሆኖባት ስትቸገር አስተውለናል፡፡ ለምን ይህ ሆነ ካልን መገፋት አንዱ ምክንያት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ እርሷ ስትገፋ ስለእምነቷ ስለባህሏ ከዚህም አልፎ ስለማህበረሰቧ ያላት አመለካከት እየተበረዘ ነው የሚሄደው፡፡ በእርሷ ላይ የደረሰው የመገፋት ችግር ከእርሷ አልፎ ለልጆቿ እንደተረፈም አስተውለናል፡፡
በአካባቢያችን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ የገፋናቸው ሰዎች አሉ፡፡ በማህበራዊ ህይወታችን ያገለልናቸው፣ በእድሩ በእቁቡ ያላሳተፍናቸው አሉ፡፡ እነእርሱ ለዚህ መሰል ችግር ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ችግራቸውን ለመመልከት እድል ስለማይኖረን ምን ተቸግረው ምን መረዳት እንዳለባቸው አናውቅም፡፡ በዚህ ምክንያት ሞሰባቸው ባዶ ሆኖባቸው ይሆናል፡፡ ተማሪ ካለ በችግር ምክንያት በስርዓት ላይማር ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ ለሀገርም ለወገንም ኪሳራ ነው፡፡ እናም እራሳችንን እንደ ጥፋተኛ አይተን በቶሎ ማስተካከል አለብን፡፡
በትዳራችን ውስጥም ይህ የመገፋፋት መጥፎ አመል ይኖራል፡፡ ባል ወይም ሚስት ሳያውቁም ወይም እያወቁ ሊገፉ ይችላሉ፡፡ ተገፊው በዝምታ ውስጥ ሆኖ ሁሉንም ቢቀበልም አንድ ቀን ግን ሁሉም እንዳልነበር ሊሆንባቸው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ እንዳይሆን ሁሉም በስርዓት በማድረግ ከመገፋፋት የፀዳ ትዳር መመስረትና መኖር ተገቢ ነው፡፡
መገፋት መገፋፋትን ከዚያም መከፋፈልን የሚያመጣ የድህነት በር ከፋች ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጲያውያን ግልፅ ጉዳይ ነው፡፡ ታሪካችን በአብዛኛው የመገፋፋት ነው፡፡ አንዱ ሌላኛውን ሲገፋው ስለኖረ አሁን ድረስ የመገፋፋት በሽታው አለቀቀንም፡፡ ይህ አሁን ድረስ ያለቀቀን በሽታ ከዚህ በላይ መሄድ ስለሌለበት መቆም አለበት፡፡
ሰዎች መልካም ያልሆነ ሐሳብ አስበው መልካም ያልሆነ ድርጊት ለመስራት የሚበቁት ሲገፉ ወይም የተገፉ መስሎ ሲታያቸው ነው፡፡ አንድ አንዶች ነገን ማሰብ አቁመው ስለ ትላንት ብቻ የሚያስቡት ስለተገፉ አሊያም የተገፉ ስለሚመስላቸው ነው፡፡ ለመበቀል አስበው “ሂሳብ እናወራርዳለን” ብለው የሚነሱት እራሳቸውን የተገፉ አድርገው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ወንድምህ ሊበቀልህ የሚያስበው ገፍተኸው ከሆነ ወይም የገፋኸው አድርጎ የሚያስብ ከሆነ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ የሚሆነው ተቀራርቦ ከልብ መነጋገር ነው፡፡
ይቺ ሀገር መረጋጋት ያልቻለችው እራሳቸውን የተገፉ አድርገው በሚያስቡ ቡድኖች ነው፡፡ በቤት ውስጥ ካሉት ልጆች መካከል ለቤተሰብ አስቸጋሪ የሚሆነው እራሱን የተገፋ አድርጎ የሚያስበው ነው፡፡ ማህበረሰቡን ለትርምስ የሚዳርገው እራሱን የተገፋ አድርጎ የሚስለው ነው፡፡ የሰውን ልጅ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ እየከፋፈሉ ይችን ሀገር ሰላም አልሰጣት ያሉት ስለመገፋት እያወሩ ነው፡፡ ፖለቲከኞቻችን እንኳን ንግግራቸው ወደፊት ስለሚሰሩት ስራ ሳይሆን ከኋላ ስለነበረው መገፋፋት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ነውጥን እንጅ ለውጥን ሊያመጣ አይችልም፡፡